"ለስደት ፍቅሩ የለኝም፤ አውስትራሊያ የመጣሁት አጋጣሚዎች ስላስገደዱኝ ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ ሳልመለስ በፊት ወድጄው የኖርኩበት ሀገር ነው" ወ/ሮ ነኢማ ሙዘይን መሐመድ

Neima M Mohammed.png

Neima Muzein Mohammed, Founder and CEO of Yimeleketegnal Charity Organisation. Credit: SBS Amharic

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

ወ/ሮ ነኢማ ሙዘይን መሐመድ፤ ለአዕምሮ ሕመምተኞች አገልግሎት ሰጪ የሆነው ይመለከተኛል በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። ከውልደትና ዕድገታቸው እስከ በጎ አድራጎት ድርጅት ምሥረታ ያለ የሕይወት ጉዟቸውን ነቅሰው ይናገራሉ።


ውልደትና ዕድገት

የወ/ሮ ነኢማ ሙዘይን መሐመድ ውልደት አዲስ አበባ ከተማ፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው።

ለወላጆቻቸው ከዘጠኝ ልጆቻቸው ውስጥ አንዷ ናቸው።

አባት በጤና አገልግሎት ዘርፍ የመንግሥት ሠራተኛ፤ እናት በአነስተኛ ንግድ ተሠማርተው የነበሩ ነጋዴ ናቸው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት የውልደት ሆስፒታላቸውን ስያሜ በሚጋራው ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ነው።

በለጋ ዕድሜያቸው ከእናታቸው የወረሱት ንቁ ሁለገብ ተሳትፎ አበረታች ልማድ ሆኗቸው በወጣቶች ማኅበራት ንቅናቄዎች፣ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችና ዘርፈ ብዙ መስኮች በበጎ ፈቃደኝነት ተሳትፈዋል።

ባሕር ማዶ ድረስም ተከትሏቸዋል።

ያልታሰበ ኑሮ በአውስትራሊያ

ወደ ሜልበርን አውስትራሊያ የመጡት በ2011 ነው።

አመጣጣቸው የእህታቸውን መውለድ ተከትሎ በጉብኘት ቪዛ በመሆኑ ለዘላቂነት የታሰበ አልነበረም።

ቀደም ሲል፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሶስት ዓመታት ኖረው የባሕር ማዶ ሕይወትን ቀምሰው ስለነበር የባሕር ማዶ ሕይወት ምኞት አልነበራቸውም።

ሆኖም፤ እህታቸውን ለማረስ ጢያራ አውስትራሊያ ያመጣቸው ነኢማ ከመቆየት ከፈረንጅ ሀገር ሕይወት ጋር ተላመዱ።

አጋጣሚውም ፈቀደና የመኖሪያ ፈቃድ አገኙ።

የሜልበርን ነዋሪ ሆኑ።

ኑሮአቸውን ለመደጎምና ክህሎታቸውንም ከፍ ለማድረግ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደው ተመረቁ።

ሀገር ቤት ሳሉ በአማተር ጋዜጠኛነት ተሳትፈው ነበርና ያን ክህሎታቸውን በሜልበርን ለሚገኝ የቢላል ማኅበረሰብ ኦንላይን ሬዲዮ ሙያዊ አስተዋፅዖ ማበርከት ጀመሩ።

ለሰባት ዓመታት አግልግሎታቸውን ቸሩ።

በእዚያም ሳይወሰኑ በZZZ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ በየሳምንቱ ሰኞ በአማርኛ ቋንቋ በሚተላለፈው ፕሮግራም ላይም ለበርካታ ዓመታት ሙያዊ በጎ ፈቃደኝነታቸውን አበረከቱ።

በግል ሕይወታቸውም በሕክምናው ዘርፍ የጥርስ ክሊኒክ ውስጥ በረዳትነት ሠርተዋል፤ በሌሎችም የተለያዩ ዘርፈ ብዙ የሥራ ዓይነቶች ተሠማርተው ኑሮአቸውን ደጉመዋል።

ከዓመታት የሕይወት ፈተናዎችና ስኬቶች በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው በፊት።

ዞሮ ዞሮ ወደ ሀገር...

ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበት አስባብ ወንድ ልጃቸው የሀገሩን ባሕልና ሃይማኖታዊ ዕሴቶች በጥልቀት እንዲረዳና ኢትዮጵያዊ ማንነቱንም አጉልቶ እንዲያውቅ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ እንዲያድግ አድርገው ስለነበር እናታዊ ጉብኝት ለማድረግ ነው።

የኮቪድ - 19 መከሰት በእሳቸውና የልጃቸው ውጥን ላይ ዝመት አሳደረ።

ልጃቸው ወደ አውስትራሊያ መመለስ ፈለገ፤ እናት ነኢማ "የለም" ብለው እሳቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

ተገናኙ። አንድ ላይ ሆኑ።

ዳግም አዲስ የኑሮ ትልም መተለም ያዙ።

የነበራቸውን የጥርስ ሕክምናና የጋዜጠኛነት ሙያዎች መዘኑ።

በረዳት ጥርስ ሕክምና ሙያ ገቢ ራሳቸውንና ልጃቸውን ማስተዳደር እንደማይችሉ ተገነዘቡ።

ፊታቸውን ወደ ጋዜጠኛነቱ አዞሩ።

ጥቂት ቆይተው በየሳምንቱ እሑድ መረጃ አቅራቢ፣ አስተማሪና አዝናኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጀመር ቻሉ።

ልጃቸውን እያስተማሩ፤ ሙያቸውን መከወኑን ቀጠሉ።

እንዲያ እያለ፤ ከአንድ ቤተሰብ ሶስት ወንድማማቾች የአዕምሮ ጤና እክል እንዳለባቸው ሰሙ።

ጉዳዩ አሳሰባቸው።

ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሰላሰሉ።

ችግሩን ለሕዝብ በማድረስ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ወሰኑ።

በቴሌቪዥን ስርጭት ፕሮግራማቸው የጤናና ማኅበራዊ ጉዳይነት አፅንዖት ሰጥተው አቀረቡት።

በሕዝብ ዘንድ ሰሞነኛ መነጋገሪያ ለመሆን በቃ።

ሌሎች ተመሳሳይና የከፉ የአዕምሮና የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ችግሮች በተለይ ከእናቶች ዘንድ በስልክ እየጎረፉ መጡ።

ጥቂቶቹን እገዛ ጠይቀው አሳከሙ።

ሆኖም፤ የችግረኞቹ ብዛትና እገዛው መሳ ለመሳ አልሔድ አለ፤ የእገዛ እጥረት ገጠማቸው።

ቆም ብለው አሰቡ።

አግባብ ካላቸው ወገኖች ጋር መከሩ።

በአዕምሮ ሕሙማን ላይ ለማተኮር ወሰኑ።

በወርኃ ጥር 2014 ከብዙ ውጣ ወረድ በኋላ ተልዕኮውን ይህንኑ ግዙፍ የጤናና ማኅበራዊ ችግር መቅረፍ ያደረገ የ "ይመለከተኛል በጎ አድራጎት ድርጅት" ለማቆም ቻሉ።
YCO.png
Credit: YCO

የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ለበቃ አስተዋፅዖ አድራጊነት ለማብቃት ርብርቦሾች ተካሔዱ።

ሁለት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 400 ያህል ወጣቶች በበጎ አድራጎት ድርጅቱ አማካይነት አስፈላጊውን አገልግሎቶች አግኝተው አገግመው ለመውጣት ቻሉ።

የይመለከተኛል በጎ አድርጎት ድርጅትን እርዳታ የሚሹ ወጣቶች እየበዙ መጡ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አውስትራሊያ ሳይዘልቁ ከ3,500 በላይ የድርጅታቸውን እገዛ ለማግኘት በተጠባባቂነት በቆይታ ባህር መዝገብ ውስጥ ሠፍረው ይገኛሉ።

የይመለከተኛል የበጎ አድራጎት ድርጅት አቅም የሌለው፤ ግን ከአቅሙ በላይ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው
ወ/ሮ ነኢማ ሙዘይን መሐመድ፤ የይመለከተኛል በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ
በቀጣዩና የመቋጫ ክፍለ ዝግጅታችን የበግ አድራጎት ድርጅቱ እንደምን አገልግሎቶቹን እንደሚያበረክት፣ የአዕምሮ ሕመም ስር መስደድና ስለሚያሹ እርዳታዎች አንስተው ያስረዳሉ።






Share