"በ'ውጫሌ ውል' ተውኔት መክፈቻና መዝጊያ ወቅት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ፈንቅሎ የወጣ የጋለ ሀገራዊ ስሜት ነበር" ተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና

TGH Patriot.png

Artist Tesfaye Gebrehana (C). Credit: Supplied

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

ተዋናይ፣ ደራሲ፣ አዘጋጅና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገብረሃና፤ በቀዳሚ ክፍለ ዝግጅታችን ውልደትና ዕድገቱን፣ የቀለም ትምህርትና የትወና ጅማሮውን ነቅሶ ግለ ታሪኩን በከፊል አውግቷል። ወደ ቀጣዩ ግለታሪክ ትረካው ያመራው እንደምን ከአንጋፋ የጥበብ ሰዎች ጋር ለመድረክ እንደበቃ በማንሳት ነው።


በአንጋፋዎች መድረክ

ተስፋዬ ገብረሃና፤ በአንጋፋው ደራሲ፣ ተዋናይ፣ አዘጋጅና ዳይሬክተር መላኩ አሻግሬ ክንፍ ስር ሆኖ ልምድ መቅሰም ያዘ።

በመሃል አራዳ ሳይወሰን በየክፍለ አገሩ የጥበብ ማዕዱን የሚያቋድሰው የተውኔት ቡድን አካል ሆነ።

በእግር ተጉዘው፣ መብራት አልባ መንደር ዘልቀው፣ በገልባጭ መኪና ላይ ቆመው፣ የአማርኛ ቋንቋን ለማይሰሙ ታዳሚዎች ሳይቀር እነሆን ብለዋል።

አድናቆትንም በእጅጉ አትርፈዋል።

ትወናቸው በሲቪሉ ኅብረተሰብ ዘንድ ውስን አልነበረም።

ጦር ካምፕ ድረስ ዘልቋል።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የመድረክ ማዕዳቸውን አጋርተዋል።

ተስፋዬ ገብረሃና፤ በመልካሙ የብዕር ዘንገኛ መላኩ አሻግሬ ተደርሶ በተክሌ ደስታ በተዘጋጀው "አንድ ጡት" ተውኔት ላይ ተሳትፏል።

መድረኩን የተጋራው ግና ከወቅቱ የመድረክ ፈርጦች ጋር ነበር።

ከዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ጌትነት እንየው፣ አስናቀች ወርቁና ዘነበች ታደሰ ጋር።

በአንድ መድረክ ትዕይንት ፤ በአንድ ቀዬ ጉዞና በመዲናይቱ ብቻም የተገደበ አልነበረም።

የሰሜን፣ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያን አካል አዳርሰዋል።

አሰብ ሳሉ የኢሕአዴግ ሠራዊት ወደ መሀል ኢትዮጵያ መግፋት ተነገረ።

እነ ተስፋዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

የተስፋዬ ክህሎት የመላኩ አሻግሬንና ተክሌ ደስታን የጥበብ ቀልብ ብቻ ገዝቶ አለመቅረቱን ዋቤ አስነቀሰ።

ለዓለምፀሐይ ወዳጆም ዓይነ ገብ ሆነ።

ያም ለብሔራዊ ቲአቲር ተቀጣሪ ባለሙያነትና የምኒልክን ገፀ ባሕሪይ ተላባሽነት አበቃው።
Tesfaye GH National Theatre.png
Artist Tesfaye Gebrehana (L). Credit: Supplied

የውጫሌ ውል

የብሔራዊ ቲአትር አካል በሆነ በ15ኛው ቀን በሻምበል ታምራት ተደርሶ በበኃይሉ መንገሻ የተዘጋጀው "የውጫሌ ወል" መሪ ተዋናይ ሆኖ ተመረጠ።

የአፄ ምኒልክን ገፀ ባሕሪይ ተላብሶ መድረክ ላይ ግዘፍ እንዲነሳ።

ከደስታ ይልቅ ድንጋጤ አደረበት።

'ምኒልክና እኔ ምንና ምን?' በሚል ዕሳቤ።

ታሪክ ለሚያክብሩትና በውል ለሚገነዘቡት ኃላፊነቱ ሀገርን በጫንቃ የመሸከም ያህል የከበደ ነውና።

እናም የተግባረ አልህቆት ወዳጁን ጌትነት እንየውን አማከረ።

አበረታች ምክር ቸረው።

ተስፋዬ የምኒልክን ገፀ ባህሪይ ድርሻ አጥንቶ ጨረሰ።

ከሀገረ ኢትዮጵያ ዐልፎ የአንደኛው ዓለም ጦርነት ታሪክና ለዓለም ጥቁር ሕዝብ የነፃነት አርማነት አስባብ የሆነውን "አንቀፅ 17" ታሪካዊ ኃላፊነት ተሸከመ።

መድረክ ላይ ነገሠ፤ ምኒልክን ሆነ።

በሰላሙ ጊዜ "እምዬ" ተብሎ ተጠራበት፤ በክተት ወቅት "እምቢኝ ለሀገሬ፤ እምቢኝ ለነፃነቴ" አለበት።

በአያሌ ኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደምና ሰማዕትነት ፀንታ የቆየችውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ አውለበለበ።

ልብን ፈንቅሎ በወጣ ኢትዮጵያዊ ስሜት "አበጀህ" ተባለ።

ዝናን አተረፈ፤ መልካም ስምና ሞገስ ተላበሰ።

ከ "ውጫሌ" ወደ "አባትየው" ተሻገረ።

ደመቀበት።

የተዋናይ ተስፋዬ ገብረሃና ተረካ በእዚሁ አልተቋጨም በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን በሎሬየት ፀጋዬ ገብረመድኅን የጥበብ ልጅነት "ሃምሌት"ን ሆኖ
ያወጋል።




Share