"ለመላ ኢትዮጵያውያን ለአዲሱ ዓመት የምመኘው አንድነትን ነው፤ አንድ ካልሆኑ ዕድገት የለም፤ አንድነት ኃይል ነው" እማማ አኒ ማርሴሩ አታሜይን

Anni M Atamain.png

Emama Annie Marcerou Atamain. Credit: SBS Amharic

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

እማማ አኒ ማርሴሩ አታሜይን፤ ቦርቀው ያደጉባት፣ ፊደል የቆጠሩባት፣ ተኩለው የተዳሩባትንና ልጆች ያፈሩባትን ሀገረ ኢትዮጵያ ለቅቀው ከወጡ የአንድ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ዕድሜ አስቆጥረዋል። የኢትዮጵያ ፍቅረ ነበልባል ግና አሁንም ድረስ ልባቸው ውስጥ ይንቦገቦጋል፤ ትዝታዎቿም ዓመታት ሳያደበዝዟቸው ግዘፍ ነስተው ከአዕምሯቸው ተቀርፀው አሉ።


ከተርክዬ ወደ ኢትዮጵያ

ለእማማ አኒና ኢትዮጵያ የዕድሜ ልክ የፍቅር ቁርኝት መነሻ የእናታቸው አባት - አያታቸው ሌቮን ያዚጂያን ናቸው።

በተርክዬ - አርሜንያ ግጭት ሳቢያ ወደ ግብፅ ተሰደዱ።

ግብፅ ሳሉም ስለ ኢትዮጵያ መልካምነት ሰሙ።

አላመነቱም፤ እብስ ብለው ኢትዮጵያ ገቡ።

ወቅቱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነበር።

ጥቂት ቆዩ። የሌቮን ያዚጂያን እጅ በሥነ ስዕል የተጠበበ ነበርና ለአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት እጅ ነሺነት አበቃቸው።

ምኒሊክ ለአድዋ ዘመቻ አብሯቸው ዘምቶ፤ የድላቸው ኃይል ሆኖ የተመለሰውን ቅዱስ ጊዮርጊስን አሰቡ።

ያዚጂያንን የአራዳ ጊዮርጊስን በቅብ ሥራቸው እንዲያስውቡ ጠየቁ።

በደስታና በሙሉ አገልጋይነት መንፈስ የአዲስ አበባውን የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በብሩሻቸው አስዋቡ።

በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ሞገስ ተላበሱ።

ቤተሰብ አልባነታቸውን ልብ ያሉት አፄ ምኒልክ ሌቮን ያዚጂያንን "ምነው
ብቻህን? ልዳርህ እንጂ" አሏቸው።

በንጉሠ ነገሥታዊም፤ በአባታዊም አንደበት።

ያዛጂያን "ጃንሆይ፤ ቱርክ አገር'ኮ ሚስትና ልጆች አሉኝ" ሲሉ አስረዱ።

በወቅቱ በአብዛኞች ዘንድ "እምዬ" ተብለው የሚጠሩት በከንቱ ውዳሴ አልነበረምና ምኒሊክ በመልካም አንደበትና ርህራሔ ሳይወሰኑ የሌቮን ያዛጂያንን ሚስትና ሶስት ልጆች ከሀገረ ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ አስመጡ።

ባል፣ ሚስትና ልጆች ተገናኙ። ለዳግም ቤተሰብ ምሥረታ በቁ።

ያዛጂያን በብሩሽ ቅብ ብቻ አልተወሰኑም። የሥጋጃ ምንጣፍ ሥራ የእጅ ባለ ሙያም ነበሩ።

የአዲስ አበባን ሴቶችና ወንዶች አጠላልፍ አስተማሩ።

አፄ ምኒልክ ዐረፉ።

እንደታሰበው ልጅ ኢያሱ የምኒሊክን አልጋ ለመውረስ ሳይችሉ ቀሩ።

የምኒልክ ሶስተኛ ልጅ ዘውዲቱ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሆኑ።

ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆነው ተሰየሙ።

ከ13 ዓመት ተኩል ንግሥና በኋላ የንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱን ማረፍ ተከትሎ ተፈሪ መኮንን ተቀብተው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስመ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት ሆኑ።

የእማማ አኒ አያት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኃላፊ ሆነው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ተሾሙ።

ቆይቶም የኢትዮጵያና የጣልያን ሁለተኛው ጦርነት ተጀመረ።

የጣሊያን ወራሪ ኃይል አዲስ አበባ ገባ።

ፍልሚያ፣ ሞትና ስደት ተከተለ።

ስደት

የእማማ አኒ እናትና አጎቶች ሀገር ለቅቀው እንዲወጡ በጣሊያን ታዘዙ።

በስደት ጂቡቲ ገቡ።

የእማማ አኒ አክስት ጂቡቲ ፈረንሳዊ ባል አግብተው ይኖሩ ነበርና እዚያ ተጠለሉ።

ያኔ አኒ ማርሴሎ አታማይን ገና አልተወለዱም።

ጂቡቲ የገቡት ላጤዋ በኋላ የአኒ እናት ለመሆን የበቁት ወ/ት ሐና ከአንድ ፈረንሳዊ የጂቡቲ ጎልማሳ ጋር ተዋወቁ።

ተፋቀሩ። ተጋቡ። አኒ ጂቡቲ ተወለዱ።

በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ወቅት አያት ሌቮን ያዛጂያን ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

አንድ ቀን ከያዛጂያን ጋር አዲስ አበባ ቀርተው የነበሩት ባለቤታቸውን አንድ የጣሊያን ወታደር ቤታቸው ግድግዳ ላይ ሰቅለውት የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ፎቶግራፍ እንዲያወርዱ አዘዛቸው።
gettyimages-79038505-612x612.jpg
Addis Ababa, Ethiopia, 1954, A portrait of Emperor Haile Selassie, the King of Abyssinia, pictured sitting in his audience chamber. Credit: Popperfoto/Popperfoto via Getty Images

የያዚያጂን ባለቤት ግና "ትገድለኛለህ እንጂ ፎቶግራፋቸውን አላወርድም። የኔ [ንጉሥ] አባባ ጃንሆይ ናቸው። እኔ ሙሶሎኒን አላውቅም" ሲሉ በቁርጠኛነት አምርረው ተናገሩ።

የጠብመንጃ አፈሙዙ በቅፅበት ሊዞር፤ ላንቃውም ጥይት ተፍቶ ሕይወት ሊነጥቅ የሚችለውን መሳሪያ ያነገበው የጣሊያን ወታደር ገፍቶ ሳያስገድዳቸው ሔደ።

የሁለተኛው ዓለም ጦርነትም አከተመ።

ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ

ጂቡቲ የተወለዱት አኒ ከወላጆቻቸው ጋር ለኢትዮጵያ ምድር በቁ።

አኒ ትምህርታቸውን ሊሴ ገብረማሪያም ትምህርት ቤት ጀመሩ።

ጥቂት እንደቆዩም ወላጆቻቸው ወደ ፈረንሳይ ላኳቸው።

ከእዚያም ወደ አየርላንድ ሔዱ።

እንደ ወጡ አልቀሩም። እ.አ.አ በ1961 ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

አዲስ አበባ በረከቷን ቸረቻቸው። ከአቶ ካቺክ ጋር ተዋወቁ።

ተፋቀሩ። ትዳር መሠረቱ።

የሁለት ወንዶች ልጆች እናት ለመሆንም በቁ።

የፖለቲካው አቅጣጫ መስመር መቀየር ሻተ።

የንቅናቄ አየር

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አየር የተማሪዎች ንቅናቄን ወደ ግራ ማንፈስ ያዘ።

አኒ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አውስትራሊያ መጡ።

ሁለት ዓመት ቆይተው ወላጆቻቸውን ጥየቃ ወደ ኢትዮጵያ ከእነ ልጆቻቸው ተመለሱ።

ወላጆቻቸው አዳማ / ናዝሬት ላይ "እቴጌ መነን ሆቴል"ን ከፍተው ጠበቋቸው።

እናታቸው አስተማሪ ነበሩና በሳምንት አንድ ጊዜ ለተማሪዎቻቸው ምግብ እየሠሩ ያበሉ ነበር።

እንዲያ ሳለ፤ የተማሪዎች ንቅናቄ ገንፍሎ ወጣ።

አመፅ ተቀሰቀሰ።

ከእማማ አኒ ወላጆች እጅ የጎረሱ ውለታ አይረሴ ተማሪዎች፤

"ሎሚ ተራ ተራ
የእማማን ቤት አደራ" ብለው ስንኝ ቋጠሩ።የግርግሩ ሰለባዎች እንዳይሆኑ ወዳጅነታቸውን በመግለጥ።

የግርግሩ ሰለባዎች እንዳይሆኑ ወዳጅነታቸውን በመግለጥ።

የእማማ አኒ እናትም እንደ መምህርትነታቸው ተማሪዎቻቸውን እንደ ልጆቻቸው ይመለከቱ ነበርና ፖሊስ ሲከተላቸው ደብቀው፤ አብልተው ይሸኙ ነበር።
Students movement 1974.png
Police officers watched a student demonstration in Addis Ababa on April 25, 1974, a few months before Emperor Haile Selassie's September 12, 1974 deposition. Credit: AFP via Getty Images
የአኒ እናት የንጉሣዊው ቤተሰብ አካል ባይሆኑም የቤተሰብ ያህል ቅርብ ነበሩ።

አብዛኛውን የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልጆች ግቢ ውስጥ ከእነ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር እየተጫወቱ ነበር።

መጠሪያ ስማቸው ሐና ቢሆንም፤ ብልህነታቸውን የሚያደንቁት ንጉሠ ነገሥት ግና የሚጠሯቸው "ሉሌ" እያሉ ነው።

ያስቡላቸው ነበር።
Hana and Emperor .png
Haile Selassie I, Emperor of Ethiopia (L) and Emama Annie's Mother Hana (R). Credit: AM.Atamain
የተማሪዎቹን ንቅናቄ ተከትሎ ሆቴላቸው ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ካሣ ሊከፍሉ ጠይቁ።

የወ/ሮ ሐና ምላሽ ግና "ልጆቹ ሆቴሌ መጥተው ምግብ በልተው ሔዱ እንጂ ምንም ያደረሱት ጉዳት የለም፤ ካሣ አልሻም" የሚል ነበር።

እማማ አኒም ከእነ ልጆቻቸው ወደ አውስትራሊያ ተመለሱ።

የለውጥ እርምጃው ክረትና ፍጥነት ጨመረ።

አብዮት

የሥርዓት ለውጥ ተካሔደ።

ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የአፄ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓተ መንግሥት ለመጨረሻው የዘውድ ሥርዓትነት ዳረገ።

በትረ ስልጣኑን ጨበጠ።

ዘውድ በሪፐብሊክ ተተካ።
gettyimages-129535368-612x612.jpg
Haile Mariam Mengistu (3rd-L), Ethiopian leader and the chairman of the Provisional Military Administration Council (1977-87) and future Ethiopian President (1987-91), Ethiopian General Teferi Bante (C), Chairman of the Military Council, and Ethiopian revolutionary leader Atnafu Abate, review a military and students' parade 29 December 1974 in Addis Ababa. Credit: J. M. BLIN/AFP via Getty Images
የአኒ እናትና አባት ንብረት ተወረሰ።

የሕይወት ዘመናቸውን የኖሩባትን ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ጥለው ወንድ ልጃቸው ወደሚኖርባት ፈረንሳይ ተሰደዱ።

እርግጥ ነው፤ ወ/ሮ ሐና ከልዕልት ተናኘ ወርቅ፣ ልዕልት ሣራና እቴጌ መነን ጋር የተጋሯቸውና የሀገረ ኢትዮጵያም መልካም ትውስታዎች ግና ከአእዕምሯቸው አልተፋቀም። ከልባቸው አልወጣም።

ቅርስ አድርገውት ቆዩ።
Hana and Menen.png
Mennen Asfaw, Empress of Ethiopia (C) and Annie in her mother Hana's arm (L). Credit: AM.Atamain
የእማማ አኒ እናትና አባት ቀሪ የሕይወት ዘመን ፓሪስ ከተማ በስደት አበቃ። ዐረፉ።

እንደ ወላጆቻቸው ሁሉ የእማማ አኒ የኢትዮጵያ ትዝታ ዛሬም ድረስ ጉልህ ነው። አዲስ ነው። አልተለወጠም።

ይትባህሉ "ነብር ዝንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን አይለውጥም" እንዲል።
ኢትዮጵያ የቆዳዬ አካል ናት። የፍቅር ቁርኝት ነው ያለን፤ ልቤን ያሞቃል።
እማማ አኒ ማርሴሩ አታሜይን
እማማ አኒ፤ ምንም እንኳ ከሀገረ ኢትዮጵያ ከወጡ ከአምስት አሠርት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥሩም፤ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያን ምግቦች አሰናድተው ይመገባሉ።

ከልጆቻቸው ዐልፎ ተርፎም የልጅ ልጆቻቸው እንጀራ በወጥ ይበላሉ።

እማማ አኒ የሀገር ልብስም አላቸው።

ዘንድሮ ሜልበር ከተማ በሚከበረው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ቅበላ ዝግጅት ላይም ለመገኘት አስበዋል።

ለመላ ኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው "አንድነት፣ አንድነት፣ አንድነት" ነው።












Share