የነባር ዜጎችን ባሕላዊ መድኃኒት ጥበብ ሞገስ ማላበስ

Debbie Watson.jpg

Traditional healer Debbie Watson

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

የነባር ዜጎችን ባሕላዊ መድኃኒት ዕውቀት መረዳትና ከበሬታንም መቸር፤ ጥንቃቄ የተመላበት ክብካቤን ለሚሻው ሁሉን አቀፍ የዘመናዊው ጤና ክብካቤ አወቃቀር ቁልፍ ሊሆን ይችላል።


አንኳሮች
  • ለነባር ዜጎች ጤና ሁሉን አቀፍ ፅንሰ ሃሳብ፤ ውስብስብ አካላዊ መስተጋብር፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ደህንነት ነው።
  • ባሕላዊ መድኃኒት ተዳሳሽና መንፈሳዊ ዝንቅነትን የተላበሰ ነው።
  • ባሕላዊ ፈዋሾች ዕውቀትና ተፈውስ ክህሎቶችን የወረሱት ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ ነው።
  • ባሕላዊ መድኃኒትና ዘመናዊ መድኃኒት እጅ ለእጅ ተያይዘው በመሥራት ባሕላዊ ጥንቃቄን ለሚሹ ጉዳዮቻቸው ሕክምናን ይቸራሉ።
ለነባር ዜጎች፤ ጤና ከደዌ ወይም ሕመም ነፃ መሆን ብቻ አይደለም። የአካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ደህንነትን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ባለ ፈርጅ መስተጋብራዊ ፅንሰ ሃሳብ ነው።

እኒህ የነባር ዜጎች ባሕላዊ መድኃኒቶች አካላዊ ሕመሞችን መፈወስ ላይ ብቻ ያተኮሩ አይደሉም፤ ዘርፈ ብዙ የደህንነት ማዕዘናትን ሚዛን ለማስጠበቅ የሚጥር ነው።

የሉትሩዊታ ሰሜናዊ ምሥራቅ ሩዉላዌይ ሴት ሐኪም አላና ጋል ከልጅነታቸው አንስቶ ለባሕላዊ መድኃኒት የጋለ ስሜት ያላቸው ናቸው።

“አገር ቤት፤ የተለያዩ ተፈጥሯዊ መድኃኒቶችንና የሕክምና ዘዴዎችን፣ መንፈሳዊና የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችን መጠቀም ትልቁ የሕይወቴ አካል ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
Dr Alana Gall.jpg
Dr Alana Gall
በሳውዘርን ክሮስ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሯዊ ሕክምና ድኅረዶክትሬት ተመራማሪ ሲሆኑ፤ እንዲሁም የነባር ዜጎች ባሕላዊ ሕክምና ማሟያና ማዋሃጃ ሕክምና ቅንጅት ዳይሬክተር ኃላፊነትን አክሎ በርካታ የኃላፊነት ሚናዎች አሏቸው።

"የጫካ መድኃኒት" የሚለው አጠራር በአብዛኛው ከባሕላዊ መድኃኒት ጋር ተዛብቶ መጠራት ሰዎች ባሕላዊ መድኃኒት ምን እንደሁ ሊኖራቸው የሚገባውን ግንዛቤ ውስን እንዲሆን እንደሚያደረግም ይናገራሉ።

ሰዎች ስለ እነሱ ሲያስቡ እንደ አየር የሚሳቡ፣ የሚዋጡ ወይም በአካል የሚዳሰሱ አድርገው ለማሰብ ይሞክራሉ።

ይሁንና "የእኛ መድኃኒቶች ከእዚያ የዘለሉ ናቸው"

“ባሕላዊ መድኃኒቶች የፈውስ ሥነ ሥርዓቶችን፣ መንፈሳዊ መድኃኒትንና ልማዳዊ ፈዋሾችን ያካተቱ ናቸው” ይላሉ።
እንዲሁም፤ ሀገራችንን፣ ምድራችንንም እንደ ፈዋሾች አድርገን እንመለከታለን። እናም የመድኃኒት አገር አለን። እናም አሁን ሰዎች የእኛን የዕውቀትና ትግበራ መንገዶች የሚናገሩት እኒያን ሁሉ መሠረት በማድረግ ነው።
ዶ/ር ኤላና ጋል

ባሕላዊ ፈዋሾች

ዴቢ ዋትሰን፤ በደቡብ አውስትራሊያ ፒፓልያትጃራ ምድር አናንጉ ፒትጃንትጃራ ያንኩንትጃትጃራ ንጋንካሪ ወይም ባሕላዊ ፈዋሽ ናቸው።

የንጋንካሪ ፈዋሾች የሰብዓዊ ፍጡር አካል ከመንፈስ ጋር ሁነኛ ተያይዥነት ያለው ነው አድርገው ስለሚመለከቱ እኛን በማገናኘት ፈውሳዊ እገዛ አድራጊ ናቸው።

"በእጆቼ ሰዎችን እፈውሳለሁ። ውስጣቸውን እመለከታለሁ፤ ውስጣቸው ያለውን ኃይልና ምን እንዳለም እረዳለሁ፤ እናም መንፈሳዊ ተግባርን እተገብራለሁ" ይላሉ።

ወ/ሮ ዋትሰን መንፈስ ሥፍራውን ስቶ ወይም ተጋርዶ ከሆነ ሕመም፣ ጭንቀትንና ሌሎች የሕመም ምልክቶችንም ሊፈጥር እንደሚችል ሲናገሩ፤

"መንፈስ ጉዳት አይደርስበትም" ባይ ናቸው።

ሰዎችን የመፈወስ ክህሎት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ነው።

ወ/ሮ ዋትሰን የመጡት ከረጅም የፈዋሾች የዘር ሐረግ ነው። ክህሎታቸውን ከአባታቸው የወረሱት ገና የልጃገረድ ዕድሜ ላይ ሳሉ ነው።  

"ፈዋሽ እንድሆን፤ ከቶውንም ብርቱ ፈዋሽ እንድሆን አስተምሮኛል" በማለትም ስለ ፈዋሽ ክህሎት አካካናቸው ይናገራሉ።
Debbie Watson 2.jpg
Debbie Watson
ወ/ሮ ዋትሰን በአውስትራሊያ የመጀመሪያው የነባር ዜጎች ፈዋሾች ማኅበር አናንጉ ንጋንካሪ ቲጁታኩ የነባር ዜጎች ኮርፖሬሽን ተባባሪ መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው።

ትርፍ አልባ ድርጅቱ ከፍለ ዘመናትን ያሸመገለውን የፈውስ አገልግሎት ነባር ዜጎች ለሆኑና ላልሆኑ ሰዎች በማበርከትና ድጋፉንም በመቸር ላይ ያለ ነው።

ዶ/ር ፍራንቼስካ ፓንዚሮኒ፤ የነባር ዜጎች ፈዋሾች ማኅበር ተባባሪ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲሆኑ፤ ዋነኛ ሙያቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ነው።

የነባር ዜጎች ባሕላዊ መድኃኒትን አስመልክቶና የጣሊያን ምሁራዊ ጥናታዊ ፅሑፍ መካከል ያለው ክፍተት "ወደ አልታወቀው 'ዓለም' እንዲጠልቁ" መራቸው።

ከደቡብ አውስትራሊያ ንጋንግካሪዎች ጋር ከተገናኙና ከማኅበረሰቡም ጋር ከመከሩ በኋላ፤ ዶ/ር ፓንዚሮኒ እንዲህ ላለው አገልግሎት ተደራሽነቱ ይበልጡን ስንዱ መሆን ያለበት ስለመሆኑ ልብ አሉ።
Dr Panzironi and Debbie Watson.jpg
From left, Dr Francesca Panzironi and Debbie Watson
ስለ እውነት ሰዎች ይፈልጓቸዋል። ቃለ ንባብ ብቻም አይደለም። ሰዎች የተሻለ ስሜት ያድርባቸዋል፤ ይሿቸዋልም።
ዶ/ር ፍራንቼስካ ፓንዚሮኒ
በአሁኑ ወቅት፤ የነባር ዜጎች ፈዋሾች ማኅበር ባሕላዊ ፈዋሽነት ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን አስችሏል፤ ከጤና አገልግሎቶች እስከ ማረሚያ ቤቶች፤ ሌሎች መማሩንና በሂደቱ ውስጥ ማለፉን ለሚሹ ተቋማትም አገልግሎታቸው ክፍት ነው።

ምንም እንኳ ባሕላዊ ፈውስ የሥነ ሕይወት ሕክምና ሞዴልን የሚተካ ባይሆንም "እጅ ለእጅ ተያይዞ ሊሠራ ይችላል" እንዲሁም በእጅጉ ጥንቃቄ ለሚያሻቸው ጉዳዮች ተጨማሪ እገዛን እንደሚቸር ዶ/ር ፓንዚሮኒ ይናገራሉ።

“እጅ-ለእጅ ተያይዞ ሊሠራ ይችላል”

ብሬት ሮውሊንግ የባኖሪና ማቶራ ሰዎች ዝርያ ሲሆኑ፤ የመድኃኒት ተንታኝም ናቸው።

ባሕላዊ መድኃኒትና ዘመናዊ መድኃኒት በተቃራኒ ያሉ ቢሆንም፤ ሁለት የተለያዩ ልዩ አተያዮቻቸው እንዳሉ ሆነው አንዳቸው ካንዳቸው ጋር ይደጋገፋሉ።
አንደኛው፤ ከግብረገብ ምስጢራችን ጋር የአስተምህሮት አፈ ታሪካችን ሲሆን፤ ሌላኛው በነጮች መንገድ የዳታና ትንታኔ አሠራር ነው። ሁለቱ ምሰሶዎች አንዳቸው ላንዳቸው ሞገስ በሚሆኑበት፤ ግና በጣሙን ተቃራኒ ከሆኑ መንገዶች ላይ የቆሙ ናቸው።
ብሬት ሮውሊንግ
ለምሳሌ፤ ፓራሲታሞል የዘመናዊ ሳይንስን ዳታና ትንታኔ መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ በአፈ ታሪክ ሲወራረድ የመጣው ባሕላዊው መድኃኒት በበኩሉ ልክ እንደዚያኛው ፍቱን በሆነ ሁኔታ ሁለት ከቶውንም የተለያዩ ዕይታዎች ኖሯቸው ግና በአንድ ነጠላ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ናቸው።
Brett Rowling.jpg
Brett Rowling
አቶ ሮውሊንግ “ከዘመን መጀመሪያ አንስቶ ያለን ነን። ሁሉም ነገር አለን። ነጮች መጥተው ነገሮች አንደምን እንደሚሠሩ እስኪያሳዩን ስንጠብቅ የነበረን አይደለንም። እኒህ ሁሉ መድኃኒቶችና ቴክኒኮች የነበሩን ነን” ይላሉ።

አክለውም፤ ጊዜው “የመንቂያ፤ ለሕዝብና ለዓለም ያን ማሳያ ነው” ብለዋል።

ዶ/ር ጋልም በበኩላቸው ከዚህ ዕውቀት ዓለም ሊያገኛቸው የሚችሉ አያሌ ትሩፋቶች አሉ በማለት ሲገልጡ፤

“እኛ አውስትራሊያ ያለን ከዓለም አንጋፋና ቀጥሎ ያለ ባለ ባሕል ነን። እናም፤ ምድርን እንደምን መከባከብ እንዳለብንና ከዓለም ጅማሬ አንስቶ መድኃኒቶችን ስንጠቀምባቸው ያሉ ክህሎቶች አሉ"

እኒያን ዕውቀቶች ከቀሰምናቸው፤ እንደ ለአንቲባዮቲክ አልሸነፍ ባይ ማይክሮቦች ላሉ የዛሬ ችግሮቻችን መፍትሔዎችን ልናበጅ እንችላለን" ብለዋል።

ዘመናዊ ሳይንስም የባሕላዊ መድኃኒቶችን ከጉዳት አድራሽነት የራቁ መሆንን ለማጣራት አስፈላጊውን ዳታና ትንታኔ ሊቸር ይችላል።

የዕውቀት ጥበቃ

የተወሰኑ ማኅበረሰባት በቂ የሆነ ጥበቃ ሳይበጅለት ዕውቀታቸውን ለማሸጋገር ያንገራግራሉ፤ አስከፊ በሆነ መልኩም አረጋውያን ያን ዕውቀት ይዘው ከእዚህ ዓለም በሞት እንደሚለዩ ዶ/ር ጋል ሲያመላክቱ፤

“እውነታው ዕውቀታችን ጥበቃ ያለው አይደለም። ይህም ማለት ጥበቃ ስለሚጎድለው ዕውቀታችንን በነፃ መስጠቱ አመቺ አይደለም” ይላሉ።

የመድኃኒት አምራች፣ የኮስሞቲክና ግብርና ኩባን ያዎች ዕውቀታችንን ውስደው ለንግድ በማዋል ይህ ነው የማይባል ትርፎችን ያጋብሱበታል ሲሉም አክለው ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

በተያያዥነትም፤ የዕውቀቱ ባለቤቶች ከጥቅሙ ተጋሪ ላይሆኑ እንደሚችሉና ዘለቄታውም እንደማያስተማምናቸው ያላቸውን ፍራቻ የሚያነሱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዶ/ር ጋል የረጅም ጊዜ ዕቅድ ዕውቀትን በመጋራት ለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ትድግና ሊውል የሚችልበትን ሥርዓተ ደንብ ማበጀት ነው።

Share