በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የወንዶች ማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ ነሐሴ 4 / ኦገስት 10 በተካሔደው ውድድር 2 ሰዓት ከ 06 ደቂቃ 26 ሰከንድ በመጨረስ የኦሎምፒክ ሬኮርድ ሰብሮ ለወርቅ ሜዳል ባለቤትነት በቅቷል።
የቤልጂየሙ ባሺር አብዲ የብር፣ ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ የነሐስ ሜዳል ለማሸነፍ በቅተዋል።
በዕለቱ የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪ የነበረው አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 39ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቅቋል።
ለማራቶን ውድድሩ ተሰላፊ ሳይሆን ተጠባባቂ የነበረው ታምራት ቶላ የኦሎምፒክ ሬኮርድ ሰብሮ ለወርቅ ሜዳል ባለቤትነት የበቃው በጉዳት ሳቢያ ከውድድሩ የተገለለውን ሲሳይ ለማን ተክቶ ነው።
የ32 ዓመቱ ታምራት ቀደም ሲል ባካሔዳቸው ውድድሮች፤ በሪዮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር፣ በ2022 ዓለም አቀፍ ማራቶንና በ2023 የኒውዮርክ ማራቶን በተከታታይ የነሐስ ሜዳሎችን ለኢትዮጵያ ያስገኘ አትሌት ነው።
ታምራት በማራቶን ያስገኘው የወርቅ ሜዳል ኢትዮጵያን በፅጌ ዱጉማ በሴቶች 800 ሜትርና በበሪሁን አረጋዊ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ባገኘቻቸው የብር ሜዳሎች ከ184 ተወዳዳሪ ሀገራት ከነበረችበት 68ኛ ደረጃ ወደ 49ኛ ደረጃ ከፍ ለማለት በቅታለች።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት አራት የኦሎምፒክ ውድድሮች ዘወትር በሚታወሱት አትሌቶቿ የወርቅ ሜዳሎችን አግኝታለች።
- አበበ ቢቂላ፤ በ1960 የሮም ኦሎምፒክ ወርቅ
- አበበ ቢቂላ፤ በ1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ወርቅ
- ማሞ ወልዴ፤ በ1968 የሜክሲኮ ከተማ ኦሎምፒክ ወርቅ
- ገዛኸኝ አበራ፤ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሎችን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ 15ኛ የውድድር ዕለት ድረስ በ32 የስፖርት ዘርፎች በተካሔዱ ውድድሮች ቻይናና ዩናይትድ ስቴትስ የሜዳል ሠንጠረዥ ላይ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን እየተፈራረቁ ደረጃዎቻቸውን ይዘው አሉ፤
- ቻይና፤ 39 ወርቅ 27 ብር 24 ነሐስ በድምሩ 90 ሜዳሎችን በማግኘት 1ኛ
- ዩናይትድ ስቴትስ፤ 38 ወርቅ 42 ብር 42 ነሐስ በድምሩ 122 ሜዳሎችን በማግኘት 2ኛ
- አውስትራሊያ፤ 18 ወርቅ 18 ብር 14 ነሐስ በድምሩ 50 ሜዳሎችን በማግኘት 3ኛ
- ኢትዮጵያ 1 ወርቅ 2 ብር በድምሩ 3 ሜዳሎችን በማግኘት 49ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።